|
(ክፍል
አንድ) ከትንሳዔ
ሲፎካከር ያለ ከጌታ ስራ
ጋር፣
አዳቆነ ሰይጣን ጳጳስ ሆነ ለሀገር፤
ፅላቱንም ሸጠ መስቀሉን አስማማ፣
ሲክድ ፈጣሪውን ጥቂት አላቅማማ።
መቋምያውን በጦር መቁጠርያ በዝናር፣
ጠበሉን በሰው ደም ታቦቱን በዶላር፤
ሰይጣናዊ ታምር አሳየ በተግባር።
በመፅሀፍ ቅዱስ ልባስ ማኒፌሰቶ አንግቦ፣
ስልጣን ቸረቸረ ተቀብሎ ጉቦ።
ማዳቆን፣ መቀሰስ፣ መዘመር፣ ማሸብሸብ፣
መፈጠር፣ መዳህም፣ መሞትም፣ ማሸለብ፤
ከእግዜር ጋር ቢሆንም ፅድቅና ኩነኔ፣
ሰይጣንስ መች ያንሳል ካመንኩበት እኔ።
መወገዝ መገረፍ መሞትም መነሳት፣
አይቀር መፈፀሙ የቃሉ የትንቢት፤
ምድር የአባቴ ነው የሳጥናኤል ዙፋን፣
ልኩነስነስ በካባው ላጊጥበት ወርቁን፤
ንስሀ እገባለሁ ሲደርስ የፍርድ ቀን።
የእርጉም ምዕራፍ ገልጠው ከመፅሀፈ ኢሕአድግ
''ሀበሻ ይበተን ዘንድ ጦቢያ እንዳታድግ
ዘር በዘር ይባላ ይሁን እንደ ዐሣ
ባንዳው እንዲኮራ ታሪክ እንዲረሳ ''
በኩራት ጠቀሱ አርዮሱ ጳውሎስ፣
ሊያጠምቁ ተነሱ ልጃቸውን መለስ።
የመለስ ጭራዎች የነጋ ፍልፈሎች፣
አድር ባዮችና ተስፋ ቢስ ከርሳሞች፤
ለክቡር ቀን ጥሪ ለመለስ ጥምቀቱ፣
ውጡና እረዱ አሉ ደም ይሙላ ጅረቱ።
በጥምጥማቸው ስር ቀይ ቆብ አጥልቀው፣
ባረኩና ሸኙ ለእርድ ቀን ውል ቆርጠው።
ጭፍራዎቹ አቅራሩ፤
ሸለሉ ፎከሩ።
መልዬ መልሹ ነገረ ብልሹ፣
ምላስ በሁለት እግር ከሳሹ ተንኳሹ!!
(አጆሀ! አጆሀ!)
የተንኮል ኮሮጆ ጥምዝ መሰሪ፣
የነገር ሸረሪት አክራሪ ደዋሪ።
(ቅልቡ የመለስ አሽከር!)
ደገሞ ለሰው ልጅ ደም ሲጠጣው ባረጀ፣
መጠመቅ ይነሰው በፈጀ ባስፈጀ።
......(ዘራፍ! ማን ብሎት ለጥፋት!)
አቅራሩ ሸለሉ ፎከሩ ዘመሩ
ከበሮውን መቱ ዘለሉ ነጠሩ
መጥምቁ አባ ጳውሎስ ገቢረ ትንሹ፣
ልጃቸውን ጠሩት መልዬ መልሹ።
በሰላሳ ነበር የኢየሱስ ጥምቀቱ፣
ውሀን ነው ያወቀ ዮሀንስ በወቅቱ፤
ውሉን ቀይሬአለሁ ባርኮቴ እንዲበዛ፣
ማተሙ እንዲፀና እንዳይለቅ በዋዛ።
በአምሳ ይሁንልህ የጥምቀት ስሌቱ፣
በህፃናትም ደም በወንዱ በሴቱ፤
የሰይጣን ነህና በደም ነው ጥምቀቱ።
ለቆሌ ውቃቢ ለአድባሩ ለአውጋሩ፣
የበጉ የዶሮ ሲሆን አይደል ጥሩ?
በሰው ደም ላጥምቅህ ላባቴ የውል ቃል፣
ቀንድ አነሰህ እንጂ ሰርቶሃል በርሱ አምሳል።
ለኔም ማዕረጌ ነህ ኩራቴና ክብሬ፣
ማስረጃ መግለጫ ለአባቴ ማደሬ።
ለጥምቀትህም ቀን ለቃልህ ማሰርያ፣
ትንሽ ትንሽ ግደል ከወዲም ከወዲያ፤
ግብር አልገባልኝም ብሎ እንዳይቆጣ፣
በጥምቀትህ ማግስት ደግሞ ነገር አምጣ።
ደም አቃባ ተግተህ እስላም ክርሰቲያኑን፣
የለኮስከው እሳት ያቃጥለው መንደሩን።
የናትክንም ልጆች ከነገር ዱላቸው፣
የአባትክንም ልጆች ሞት ደግስላቸው።
መቀሌውስ ሆነ ሀውዜን ላንተ ምንህ፣
ከበሮውን ይዞ አጆሀ!ካላለህ።
የኦሮሞውማ ብትፍቀው ብትነድለው፣
'ወልቂጡማ'ካለ 'ቢሊሱማ'አይቀረው።
ደግሞ ይሄን ነፍጠኛ ሀገር ሀገሬ ባይ፣
ሀገሩ ላይ ይሙት ዐለሙንም ሳያይ።
ጠግቦ ያላደረው ዱርዬ ቦዘኔ፣
ጥይት ለምን ይባክን ግደለው በጠኔ።
የአበሻ ልጅ ሁላ ሰልፍም እንዳይወጣ፣
ለብሌር ንገረው ቡሽንም ተቆጣ።
መጥምቁ አባ ጳውሎስ ገቢረ ትንሹ፣
ልጃቸውን ጠሩት መልዬ መልሹ።
እንግዲህ እርከሰው ሽልማት ይብዛልህ፣
እንዳትሳሳ ላገር ይጠነክር ሀሞትህ፤
ምሽትህ ለአንተ አትሁን ወዳጆችህ ይጥሉህ፣
የዘራኸው አይብቀል ፈሬህም ትካድህ
ፍቅርና ደስታም ዐይንህ አትይ ሰላም፣
ጠርጣራ ጰርጳራ እንደሆንክ አትክረም፤
በደም እንደወጣህ ይመልስህ በደም።
አሉ በለሆሳስ ታጋዩ አባ ጳውሎስ፣
ፈሪነቱን አውቀው ወኔውን ለማደስ።
በእርግማኑ ረክቶ በጥምቀቱ ቢርስ፣
መልዬም ተነሳ እያለ ወዲ አሪዮስ።
ስብሀት በረከት ሹሙ ሹማምንቱ፣
ተነሱ ዘለሉ ........... ከበሮ እየመቱ።
ድም !... ድድም.!.......... ኩስስ ኩስስ
ለሁላችን ትርፍ ....... ይኑር ነፍስ
የሰይጣን ነን.......በለን ደስ!!
ፍለጥ ቁረጥ ....... ይሙት ይርገፍ፤
እመር ...እመር......... እንገፍ እንገፍ፤
ድም....... ድል ........... እረድ ግደል፣
የአበሻ አገር ......... ትሁን ሲዖል።
ሽቅብ ሽቅብ አሉ ፈጣሪን ተጋፉ፤
ሸቀጡ ጠገቡ እንደ አህያ አናፉ።
ደም ጠማቸው መሰል ፅዋቸው ተነሳ፣
ሀገር ልትታመስ ልናይ ደግሞ አበሳ።
ከ ትንሳዔ
_________________________________________________________________
|