|
(በወለላዬ)
አዋጅ አዋጅ አዋጅ የደበሎ ቅዳጅ
በአለም ዙርያ ያለህ የሀገር ተወላጅ
ወያኔን ለማጥፋት ተጠርተሀል ግዳጅ
ጆሮ ያለህ ስማ ላልሰማው ተናገር
ዝም ብለህ አትይ አገር ስትሸበር
እድሜ ሳይወስንህ ሳትል ወንድና ሴት
ወገንህን አድን ተነሳ በህብረት
ከህዝብ ጋር ሆነህ በትግሉ ተሳተፍ
እንደየ ችሎታህ በገንዘብህ ደግፍ
የወያኔን ጥፋት ለአለም ህብረተሰብ
አሳውቅ አስረዳ ተገናኝ ተሰብሰብ
ምን እንደሚደረግ ተማከር ተወያይ
መፈክር አንግበህ ወጣ ከአደባባይ
በነጋ በጠባ ተቃውሞህን ግለጽ
አለም ይነጋገር በሰው አገር አምጽ
ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሰማህ ይሄን ቃል
ወገንህን ታደግ ጥሪውን ተቀበል
ብዙዎች በጥይት ተመተው ወድቀዋል
የቁርጥ ቀን ልጆች ተይዘው ታስረዋል
ምን እነግርሀለሁ ሰምተሀል አይተሀል
የተወለድክበት ያደክበት አገር
እየታመሰ ነው በአጋዚ ወታደር
ወገንህ በዱላ አናቱ ተገምሶ
በሰደፍ ብለውት ሽንጡ ተበሶ
በጥይት እሩምታ እየተበሳሳ
እመንገድ ላይ ቀርቷል እንደውሻ እሬሳ
ግማሹን አግዘው ወስደው ከአዲስአባ
በረሀ ጥለውት ጨረሱት በወባ
በአንድ ምላጭ ሁሉን ላጭተው በማዳረስ
ያፈሱትን ወጣት አጋልጠዋል ለኤድስ
አዋጅ አዋጅ አዋጅ የደበሎ ቅዳጅ
በአለም ዙርያ ያለህ የሀገር ተወላጅ
ወያኔን ለማጥፋት ተጠርተሀል ግዳጅ
ጆሮ ያለህ ስማ ላልሰማ ተናገር
ዝም ብለህ አትይ አገር ስትሸበር
እድሜ ሳይወስንህ ሳትል ወንድና ሴት
ወገንህን አድን ተነሳ በህብረት
ከህዝብ ጋር ሆነህ በትግሉ ተሳተፍ
እንደየ ችሎታህ በገንዘብም ደግፍ
ፕሮፌሰር መስፍን በስተርጅና እድሜአቸው
ዶክተር ሀይሉ አርአያ እንጂነር ግዛቸው
ኮነሬል ታምሩ ሻለቃ ጌታቸው
ዶክተር በፍቃዱ ብርሀኑ ነጋ
መሪው ሀይሉ ሻውል ወድቀዋል ካደጋ
ያዕቆብ ወልደማሪያም ክፍሌ ጥግነህን
እያሰቃየነው አስሯቸው እስካሁን
ደበበ እሸቱና ብርቱካን ሚደቅሳ
እየቆጠሩ ነው እስር ቤት አበሳ
ጋዜጠኞች ሁሉ ሰብስቦ ጨምድዷል
እውጪም ያሉትን ብዙዎችን ከሷል
እንዳያሳትሙም ጭራሹን አግዷል
ያሳር ቤት ሆናለች የሀገርህ ከተማ
ወጣ ከአደባባይ ድምጽህን አሰማ
በጩኸትህ ይድመቅ የፈረንጆቹ ሀገር
ያለውን ሁኔታ ለህዝቡ ተናገር
ቅመማ ቅመሞች ቡና ቆዳ መተጥ
እንዳይሸጥ ጨርሶ እንዳይለዋወጥ
ስጋ ጫት አበባ ፍጹም እንዳይገዙ
በአየር መንገዱም እንዳይጓጓዙ
ገንዘብ የሚሰጡት እርዳታ እነሲዳ
አላግባብ እንደሆን አሳውቅ አስርውዳ
የአለም መንግስታት እንዲጥሉ እቀባ
ጩኸትህ ይቀጥል ጥሪህ ያስተጋባ
የቆመ እንዳይመስልህ ግፍና በደሉ
አሁንም ቀጥሏል ማሰሩ መግደሉ
በትግልህ ግፋበት ጠንክር አታሰልስ
ወያኔ እስኪጠፋ ብን ብሎ እንደጭስ
በስደት ነዋሪው የሀይማኖት መሪ
በየቦታው ያለህ ተማሪ አስተማሪ
ገጣሚ ጸሀፊ ሙዚቃ ቀማሪ
ጋዜጠኛ የሆንክ ቃላት አሳማሪ
ድርሻህ ከፍ ያለ ነው በዚህ አዋጅ ጥሪ
አዋጅ አዋጅ አዋጅ የደበሎ ቅዳጅ
በአለም ዙርያ ያለህ የሀገር ተወላጅ
ወያኔን ለማጥፋት ተጠርተሀል ግዳጅ
ጆሮ ያለህ ስማ ላልሰማው ተናገር
ዝም ብለህ አትይ አገር ስትሸበር
እድሜ ሳይወስንህ ሳትል ወንድና ሴት
ለወገንህ ታደግ ተነሳ በህብረት
ሁልህም በሙያህ በየችሎታህ ዘርፍ
የቻልከውን አድርግ በገንዘብም ደግፍ
አዋጁን ተቀበል በጥሪው ትውሳተፍ
|